ህይወት ግዛቷ ሲጣስ
ማሳለፍ እንደ ሞት ነው፣ አንድም ሰው አይቀረው፤ ሕይወት ፣ ሞት እና ራስን ማጥፋት ራስን ማጥፋት የሠው ልጅ ከተፈጠረ ጀምሮ በሚባል መልኩ የቆየ እና የከረመ የኑሮው አንዱ መገለጫ ተደርጎ የሚቆጠር ጥንታዊ ድርጊት እንደሆነ፣ የታሪክ መዛግብት ይመሠክራሉ:: ራስን ማጥፋት በትርጓሜ ደረጃ ለመረዳት ያህል ከተረጎምነው አንድ ሠው የራሱን ሕይወት ሲያጠፋ ነው ማለት እንችላለን:: ይህ ትርጓሜ ግን ውስብስብ ከሆነው ራስን የማጥፋት ዝንባሌ እና ድርጊት አናጻር ካየነው ብዙም ገዢ ላይሆን ይችላል:: የዚህ መጽሐፍ ደራሲ ንጉሡ አጥናፉ በግል፣ ማኅበረሰባዊ በሆነ ዕይታቸው እና ገጠመኞቻቸው ተነስተው ይህን መጽሐፍ ሊጽፉ እንደተነሱ የመጽሐፉ መግቢያ ላይ ይነግሩናል:: በዋነኝነትም ሠዎች ራሳቸውን ለምን እንደሚያጠፉ ከማየታችን በፊት ያ የሚጠፋው ሕይወት ምንድን ነው? ብለው ያጠይቃሉ:: (ገጽ 15) ጥያቄው በራሱ ከባድ እና ውስብስብ መሆኑን የሚነግሩን ደራሲው፣ የበለጠ ጥያቄውን የሚያወሳስበው ደግሞ ሠዎች ይህን ጥያቄ ብዙ ግዜ የሚጠይቁት በሚጨነቁበት ወይም እሴቶቻቸው በሚጣሱበት የሕይወት አጋጣሚ ላይ በመሆኑ ነው:: የፍልስፍና ተማሪ እና ተመራማሪ ያልሆኑ ሠዎች እምብዛም እንዲህ ዓይነቱን ጥያቄ በዕለት ተዕለት ሕይወታቸው አለመጠየቃቸውን ያስተውሏል ይሉናል ደራሲው:: “ሕይወት እንደ ኦሎምፒክ ጨዋታዎች ነው:: ጥቂቶች ሜዳሊያ ለማግኘት ጡንቻቸውን የሚያጠነክሩበት፤ ሌሎች ለታዳሚው የተለያዩ ነገሮችን በመሸጥ ትርፍ የሚያገኙበት እና ብዙዎች ደግሞ እንዴት እንደሚከናወን ለማየት የሚመጡበት ነው:: ” ፓይታጎረስ የሕይወትን ትርጉም ለመረዳት፤ ትርጉምን ራሱ መረዳት አለብን የሚሉን ደራሲው ሄደን- ሄደን ህይወትን መተርጎም ላይ እንቸገራለን ይሉናል:: ይህ ደግሞ የሚሆነው በተለያየ ምክንያት ነው